የቅዱስ መታሰቢያ የትምህርትና የእግርኳስ ፋውንዴሽን

ተልእኮ-
ትምህርት እና እግር ኳስን በማጣመር በዕውቀት በስነምግባር እና በአካል ብቃት የታነጸ ኢትዮጵያዊ ወጣቶችን ማፍራትን፣

ራዕይ –
ብሩህና የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ዕውቀትና ፍላጎት ያላቸው ኢትዮጵያዊ ወጣቶች ማፍራት፣
ከልጅነታቸው ጀምሮ በትምህርት እና እግር ኳስ ዝንባሌውን ፍቅር ኖሯቸው እድሉንና አቅሙን ያላገኙ ወጣቶችን በማሰባሰብ በአካል በስነልቦናዊና የትምህርት ችሎታቸው ልቀው የሚገኙበትን ዘላቂ የሆነ ሁለገብ ሥልጠናን እንሰጣለን። ይህ ሥልጠና ወጣቶች ወደ ጎጂ ምግባር እንዳይሄዱ አስተዋጽ ኦ ከማድረጉም በላይ በቡድን እና በጋራ አስተሳሰብ ያደገ ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር ያግዛል። ከልጅነትነት በዕውቀትና በአካልና በጥሩ ስነምግባር ተኮትኩቶ ያደገ ወጣት ራሱን የሚመስል ትውልድ ለመፍጠር ፍላጎትና ችሎታ ይኖረዋል።

ፍልስፍናችን –
የቅዱስን መሻት መፈጸም ነው። ቅዱስ በህይወቱ ህልሞች ነበሩት። ቅዱስ ዓለማችን ለሰው ልጅ ውብና አስደሳች እምትሆንበትን የተሻለ መንገድ መርምሮ ለማወቅ ይተጋ ነበር። ይህን እውቀት ፍለጋ ሲነሳ እግር ኳስን ይዞ ነው። እግር ኳስ ለቅዱስ፣ ከህይወት ምርጫዎቹ ዋነኛው ነበር። ለከፍተኛ ትምህርቱ እንኳ ሲያመለክት፣ የእግር ኳስ ህልሙን ለመፈጸም መሆኑንም ጭምር ገልጾ ነው። ምክንያቱም እግር ኳስ ገንቢ አስተሳሰብን፣ የቡድንና የጋራ አመላከከትን እንዲሁም ለችግሮች መፍትሔ የመሻትን ልዩ ችሎታ ያበለጽጋል ብሎ ያምናል።

ትምህርት-
ታዳጊ ወጣቶች እግዚሐብሄር የሰጣቸውን የተፈጥሮ ጸጋ ተጠቅመው ዕውቀታቸውን እንዲያዳብሩ የሚያስችላቸውን ሁኔታዎች እናመቻቻለን። ይህን እንደ አስፈላጊነቱ ትምህርት ቤት፣ወጪዎችን ሸፍኖ ማስገንባትን እና የግል አስጠኚዎችን መቅጠርን ይጨምራል።

እግር ኳስ-
የስⶒርታዊ አካል ብቃትና ስልነቦና ለመገነባት የእግር ኳስ ዝንባሌ ያላቸውን ወጣቶች እናሰለጥናለን። የተለያዩ ቡድኖችን በማዋቀር እያንዳንዱ ተጫዋች ብቃት ለመገነባት የሚያስችል ክትትል በአሰልጣኞች ይደረጋል።ደረጃውን በጠበቀ የ እግር ኳስ ስልጠና በብሄራዊም ሆነ በፍሪካ እና ዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ወጣቶች ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጋር በመበተባበር እናፈራለን።

ምልመላ፡
ዕድሜያቸው ከ9-13 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ይመለመላሉ። ምልመላው ከትምህርት ቤታቸው ከሚገኝ የትምህርት ውጤት እና በፕሮፌሽናል አሰልጣኞች የሚረጋገጥ የእግር ኳስ ዝንባሌ ላይ የተመሰረተ ይሆናል።

ስለ እኛ-
የቅዱስ መታሰቢያ የትምህርትና እግርኳስ ማዕከል/ፋውንዴሽን?- የቅዱስን የረጅም ጊዜ ህልም ተግባራዊ ለማድረግ፣ ደረጃው ከፍ ያለ የትምህርትና የእግር ኳስ ሥልጠናን፣ እድሉን ላላገኙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ለመስጠት፣ በቅዱስ ቤተሰቦች እንዲሁም ለዓላማው ተባባሪ በሆኑ ወገኖችና ጓደኞቹ አማካይነት የተቋቋመ ነው።

የቅዱስ ሐብታሙ ለማ የሕይወት ታሪክ

ለጋውና ወጣቱ ቅዱስ ፣ ከአባቱ አቶ ሐብታሙ ለማ እና ከእናቱ ዶ/ር ዮዲት በላይ ብናልፈው በፌርፋክስ ቨርጂኒያ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር፣ ጥር 2/1991 ተወለደ። 20ኛ ዓመቱን ለማክበር አንድ ወር ያህል የቀሩት ቅዱስ፣ የሕይወት ታሪኩ አጭር ነው። ምክንያቱም ለታሪክ እሚያበቃውን ረጅም እድሜ አልታደለም። የልጅ አዋቂ ቢሆንም ታሪኩ የልጅነት ነው። በዚያች አጭር የቅምሻ ዘመኑ ግን፣ የህልፈቱን ቁጭትና ጸጸት ብቻ ትቶልን አልሄደም። ለዘለዓለም እሚቀር ጥልቅ ፣ ረቂቅ ፣ ውብና አስደሳች ትዝታውን ለወላጆቹ፣ ለቤተሰቦቹና ጓደኞቹ ትቶ አልፏል። ቅዱስ የአንድ እህቱ፣ ረድኤት ሐብታሙ ለማ ፣ ታላቅ ወንድም ሲሆን፣ ለወላጆቹ የበኩር ልጅ ነው። አስተዳደጉ በልዩ ፍቅርና እንክብካቤ ቢሆንም፣ የዚያኑ ያክልም ሁሌም ራሱን በራሱ አንብቦና ኮትኮቶ ለማሳደግ የሚጥር ባለ ብሩህ አዕምሮ ነበር።
ቅዱስ በትምህርቱ ፣ በሙዚቃ፣ በስፖርትና በተሰለፈበት መስክ ሁሉ ልቆ እየተገኘ፣ ሲሸለም ያደገ ሁለገብ ልጅ ነበር። ልዩ ችሎታውን ማሳየት የጀመረው፣ ገና በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለ ነበር። በዌፕስ ሚል ኤለመንትሪ ፣ የላቀና የተደነቀ ውጤት በማምጣቱ፣ የትምህርት ቤቱን ፕሪዚዳንት የላቀ ሽልማት (President’s Award for Educational Excellence) እስከ መቀበል ደርሷል። በሪቸል ካርሰን ሚድል ስኩልም የማዕረግ ተማሪ በመሆን ተመሳሳይ ውጤት በማግኘቱ፣ እዚህም እንዲሁ፣ የትምህርት ቤቱን ፣ የፕሬዚዳንትስ አዋርድ ተቀብሏል። በኦክተን ኃይስኩል ተመሳሳይ ጥረቶችን በማሳየት ከፍተኛ ውጤቶችን አስመዝግቧል።

ስፖርት በታዳጊው ቅዱስ ህይወት ውስጥ ልዩ ስፍራ ነበረው። ቅዱስ በልዩ ሁኔታ የተደነቀበት እግር ኳስ ቢሆንም፣ በሌሎች የስⶒርት ዓይነቶችም ተሳትፏል። ለምሳሌ በሪቸል ካርሰን ሚድል ስኩል በነበረ ጊዜ፣ መቀመጫውን በደቡብ ኮሪያ ካደረገ፣ የቴክዋንዶ ፌደሬሽን፣ የሁለተኛ ደረጃ ብላክ ቤልት ተቀብሏል ። በእግር ኳስ ስⶒርትም፣ እሱ በነበረባቸው የትምህርት ቤቶች፣ የላቁ ውጤት ከነበራቸው ክለቦች እንደ “መክሊን ሶክር ቲም”፣ ኦክተን ሃይስ ስኩል ቲም፤ ዘ መክሊን ሶከር አካዳሚ፣ እና ቤተዝዳ ሶከር አካዳሚዎች በመሳተፍ በምርጥ ተጫዋችነት ተሳትፏል። ስለ ችሎታና ጠባዩም አሰልጣኞቹም ሆነ ጓደኞቹ አሁን ድረስ ያለማቋረጥ የሚመስከሩለት ነው። በዚህ ችሎታውም፣ ወደ ዋናዎቹ ብሔራዊ የእግር ኳስ ክለቦች ለመሸጋገር ዓይን የተጣለበትና ፣ እንደ ዲሲ ዩናይትድ አካዳሚ የመሳሰሉት የእግር ኳስ ክለቦች ለመሰልጠን የታጨ ተጫዋች ነበር። በስፖርት አማካይነት በርካታ ጓደኞችን በማፍራት፣ ከስፖርት አሰልጣኞችም ጋር፣ ስለ ችሎታው ልዩ ቅርበትን፣ ትዝታና ወዳጅነትን መፍጠር ችሏል። ቅዱስ የአውሮፓና የላቲን አሜሪካን የእግር ኳስ ጨዋታዎችን በልዩ ፍቅር ይከታተል ነበር። ከልጅነቱ ጀምሮ ግን ከቸልሲ እሚያስበልጠው ቡድን አልነበረም። ይህን የኳስ ፍቅሩ እንዲፈጸምለት ወላጆቹ ብዙ ደክመዋል። ገና በ11 ዓመቱ ፣ ደቡብ አፍሪካ ድረስ ሳይቀር በመውሰድ፣ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታዎችን እንዲከታተል አድርገውታል።

ቅዱስ በየእግር ኳስ ጨዋታ ውድድሮቹ በሚያስቆጥራቸው ግቦች ብቻ ሳይሆን፣ በትምህርቱም ውጤት እሚያስቆጥር ታታሪ ተማሪ ነበር። ቅዱስ ለትምህርት ብቻ ሳይሆን ለኪነጥበብም ልዩ ፍቅርና ዝናባሌ አሳይቷል። በተለይ እንደ ፒያኖ፣ ቼሎ እና የመሳሰሉትን የሙዚቃ መሣሪዎችን ያለመታከት በትዕግስት ይጫወት እንደነበር ይታወቃል። በሚያያቸው ፊልሞችና የቴሌቪዥን ትርኢቶች ሳይቀር፣ ልዩ የሕይወት ምርጫና አመለካከት እንደነበረው ግልጽ ነበር። ዩኒቨርስቲ ኦፍ ፒትስበርግ በመግባት በሚወደው የፍልስፍና መስክ፣ በሰብአዊነት (Humanity)፣ በሥነ ምግባር (Ethics) በሞራሊቲ (Morality) ህልውና (Existence)በመሳሰሉ የትምህር መስኮች የመጀመሪያ ዲግሪውን ለመማር ቆርጦና መርጦ መግባቱም እሚያሳየው ይህንኑ ነው።

ሳቂታና ተጫዋች የነበረው ቅዱስ ፣ በልጅነቱ የጎለመሰ፣ ከዋዛና ፈዛዛ ነገሮች እየራቀ፣ ኮስተር ወዳሉ አስተሳሰቦችና ቁምነገሮች ጠልቆ እየመጠቀ የመጣ ብስል ልጅ ሆኖ መታየት ከጀመረ ቆይቷል። እሚወዳቸውን የኮሜዲ ትርኢቶችን እንኳ እንደ መሳቂያ መሳለቂያ ብቻ ሳይሆን፣ ዓለምን እንደ መታዘቢያ ጥበብ አድርጎ ይዝናናበት የነበረ ጥልቅና ረቂቅ ልጅ ነበር። የቴሊቪዥን ትርኢቶች፣ የሳይንስ ልቦለዶችና፣ የተለያዩ አዝናኝ ትርኢቶች ለቅዱስ ሁሌም የምርምር ምክንያቶቹ ነበሩ።
ቅዱስ በሀሳብ ልቆና መጥቆ በመሄድ፣ የህይወትን ፍቺና ትርጉም ለመርመር ከፍስልፍና ጥያቄዎች እሚታገል፣ ወጣ ያለ ልጅ ነበር። ቅዱስ ጠያቂ ነው። ይጠይቃል። ስለሰዎች አኗኗር፣ በተለይም ስለ ጎስቋላና ደካማ ሰዎች ህይወት ይጨነቃል። ስለ አስተሳሰቡና እምነቱም ፊት ለፊት ይሟገታል። በፍጹም አያስመስልም። የልጅ አዋቂ ሆኖ አድጓል። እናቱ እንደምትለው በክርክር ወቅት ዝም ለማለት ወይም ዝም ለማሰኘት ሲፈልግ፣ ብዙ ጊዜ እየቀለደ “እኔ ማውቀው አለማወቄን ነው” እሚለውን የሶቅራጥስን ጥቅስ ይጠቀማል።

ከወላጆቹ ጋር ዓለምን የዞረው፣ ከስፖርት እና መጫወቻ ሜዳ ላይ የቧረቀው፣ ከእህቱጋር በፍቅር የተጫወተው፣ ከእናቱ ጋር የተቃለደው፣ ከአባቱ ጋር እንደ ልጅም እንደ ጓደኛም የተላፋው፣ ቅዱስ ሐብታሙ ለማ ፣ በተስፋ የበቀለ የህልም አበባ ነበር። ዝምተኛው ቅዱስ ዝም ብሏል። ዲሴምበር 15/2018 ይማርበት በነበረው በዩኒቨርስቲ ኦፍ ፒትስበርግ ከዚያ ዓለም በሞት ተለይቷል። ልዑል ኃያል እግዚአብሔር ነፍሱን በገነት ያኑረው።

Copyright 2019 The Kidus Legacy Education and Soccer Foundation. All rights reserved. Privacy Policy